Deuteronomy 22

1የወንድምህ በሬ ወይም በግ ጠፍቶ ሲባዝን ብታየው፣ ወደ እርሱ መልሰህ አምጣለት እንጂ ዝም ብለህ አትለፈው፤ 2ወንድምህ በአቅራቢያህ ባይኖር፣ ወይም የማን መሆኑን የማታውቅ ከሆነ፣ ባለቤቱ ፈልጎት እስኪመጣ ድረስ፣ ወደ ቤትህ ወስደህ ከአንተ ዘንድ አቈየው፤ ከዚያም መልሰህ ስጠው። 3የወንድምህን አህያ ወይም ልብስ ወይም የጠፋበትን ማናቸውንም ነገር ስታገኝ እንደዚሁ አድርግ፤ በቸልታ አትለፈው።

4የወንድምህ አህያ ወይም በሬ መንገድ ላይ ወድቆ ብታየው፣ በእግሩ እንዲቆምለት ርዳው እንጂ ዐልፈኸው አትሂድ።

5ሴት የወንድ ልብስ አትልበስ፤ ወንድም የሴት ልብስ አይልበስ፤ እንዲህ የሚያደርገውን ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ይጸየፈዋልና።

6በመንገድ ስታልፍ፣ አንዲት ወፍ ጫጩቶቿን ወይም ዕንቁላሎቿን የታቀፈችበትን ጐጆ በዛፍ ወይም በመሬት ላይ ብታገኝ፣ እናቲቱን ከነጫጩቶቿ አትውሰድ፤ 7ጫጩቶቿን መውሰድ ትችላለህ፤ እናቲቱን ግን መልካም እንዲሆንልህና ዕድሜህም እንዲረዝም ልቀቃት፤

8አዲስ ቤት በምትሠራበት ጊዜ፣ ከጣራው ላይ ሰው ወድቆ በቤትህ ላይ የደም በደል እንዳታመጣ፣ በጣራው ዙሪያ መከታ አብጅለት።

9በወይን ተክል ቦታህ ውስጥ ሁለት ዐይነት ዘር አትዝራ፤ ይህን ካደረግህ፣ የዘራኸው ሰብል ብቻ ሳይሆን፣ የወይን ፍሬህም ይጠፋል።

10በሬና አህያ በአንድ ላይ ጠምደህ አትረስ።

11ሱፍና በፍታ አንድ ላይ ተፈትሎ የተሠራ ልብስ አትልበስ።

12በምትለብሰው ልብስ ላይ በአራቱ ማእዘኖች ዘርፍ አድርግ።

ጋብቻን በንጽሕና ስለ መጠበቅ

13አንድ ወንድ ሚስት አግብቶ አብሯት ከተኛ በኋላ ቢጠላት፣ 14ስሟንም በማጥፋት፣ “ይህችን ሴት አገባኋት፤ ዳሩ ግን በደረስሁባት ጊዜ ድንግልናዋን አላገኘሁም” ቢል፣ 15የልጂቱ አባትና እናት ድንግልናዋን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ይዘው በከተማዪቱ በር ወዳሉት አለቆች ይምጡ። 16የልጂቱም አባት ለአለቆቹ እንዲህ ይበል፤ “ልጄን ለዚህ ሰው ዳርሁለት፤ እርሱ ግን ጠላት፤ 17ስሟንም በማጥፋት፣ ‘ልጅህን ከነድንግልናዋ አላገኘኋትም’ ብሎኛል፤ ነገር ግን የልጄ ድንግልና ማረጋገጫ ይኸውላችሁ፤” ከዚያም ወላጆቿ የደሙን ሸማ በከተማዪቱ አለቆች ፊት ይዘርጉት። 18ከዚያም በኋላ አለቆቹ ሰውየውን ይዘው ይቅጡት፤ 19ይህ ሰው የአንዲት እስራኤላዊት ድንግል ስም አጥፍቷልና አንድ መቶ ሰቅል
ወደ አንድ ኪሎ ግራም ነው።
ብር ያስከፍሉት፤ ገንዘቡንም ለልጂቱ አባት ይስጡት፤ ሴቲቱም ሚስቱ ሆና ትኖራለች፤ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ሊፈታት አይችልም።

20ሆኖም ክሱ እውነት ሆኖ ሴቲቱ ድንግል ለመሆኗ ምንም ማረጋገጫ ማቅረብ ካልተቻለ፣ 21ገና በአባቷ ቤት ሳለች በማመንዘር በእስራኤል ውስጥ ወራዳ ተግባር ፈጽማለችና ወደ አባቷ ቤት ደጃፍ ያምጧት፤ እዚያም የከተማዋ ሰዎች እስክትሞት ድረስ በድንጋይ ይውገሯት። ክፉውን ከመካከልህ ማስወገድ አለብህ።

22አንድ ሰው፣ ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ተኝቶ ቢገኝ፣ አብሯት የተኛው ሰውና ሴቲቱ ሁለቱም ይገደሉ፤ ክፉውን ከእስራኤል ማስወገድ አለብህ።

23አንድ ሰው የታጨች ድንግል በከተማ ውስጥ አግኝቶ ከእርሷ ጋር ቢተኛ፣ 24ልጃገረዲቱ በከተማ ውስጥ እያለች አስጥሉኝ ብላ ስላልጮኸች፣ ሰውየውም የሌላን ሰው ሚስት አስገድዶ ስለ ደፈረ፣ ሁለቱንም ወደ ከተማ ደጃፍ ወስዳችሁ እስኪሞቱ ድረስ በድንጋይ ውገሯቸው። ክፉውን ከመካከልህ ማስወገድ አለብህ።

25ነገር ግን አንድ ሰው የታጨችውን ልጃገረድ ከከተማ ውጭ አግኝቶ በማስገደድ ቢደፍራት፣ ይህን ድርጊት የፈጸመው ሰው ብቻ ይገደል። 26በልጃገረዲቱ ላይ ግን ምንም አታድርጉባት፤ ለሞት የሚያበቃ ኀጢአት ምንም አልሠራችም፤ ይህ ዐይነቱ ጕዳይ፣ አደጋ ጥሎ ባልንጀራውን ከሚገድል ሰው አድራጎት ጋር የሚመሳሰል ነው። 27ምክንያቱም ሰውየው የታጨችውን ልጃገረድ ከከተማ ውጭ ስላገኛትና ብትጮኽም እንኳ ለርዳታ የደረሰላት ማንም ሰው ስላልነበር ነው።

28አንድ ሰው ያልታጨች ልጃገረድ አግኝቶ በማስገደድ ቢደርስባትና ቢጋለጡ፣ 29ሰውየው ለልጅቷ አባት አምሳ ሰቅል
ወደ 0.6 ኪሎ ግራም ነው።
ብር ይክፈል፤ ልጃገረዲቱን አስገድዶ ደፍሯታልና፣ እርሷን ማግባት አለበት፤ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ሊፈታት አይችልም።

30አንድ ሰው የአባቱን ሚስት ማግባት የለበትም፤ የአባቱንም መኝታ አያርክስ።

Copyright information for AmhNASV